You are currently viewing በሂውስተን የኢትዮጵያዊያን ሕብረተሰብ የአንድነት ማሕበር  በአቶ ሃጫሉ ሁንዴሳና በሌሎች ወገኖቻችን የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ፥

በሂውስተን የኢትዮጵያዊያን ሕብረተሰብ የአንድነት ማሕበር በአቶ ሃጫሉ ሁንዴሳና በሌሎች ወገኖቻችን የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ፥

መስከረም 19, 2013 ዓ,ም
 
የወንድማችን የአቶ ሃጫሉ ሁንዴሳን አሳዛኝ ግድያ አስመልክቶ በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ በአዲስ-አበባ፣ በአዳማ፣ በአምቦ፣ በአርሲ፣በዝዋይ፣ በቀርሳ፣ በደራ፣ በአርሲነገሌ፣ በሻሸመኔ፣ በሐረርና በሌሎችም በርካታ የሐገሪቷ ክፍሎች ውስጥ በዜጎች ላይ ዘር ተኮር አረመኒያዊ ጭፍጨፋና እንዲሁም ዜጎች በሕይወትዘመናቸው ሰርተው ያፋሯቸው ንብረቶች በሰዓታት ውስጥ ወድመው ማየታችን ለእኛ በሂውስተን ቴክሳስ አካባቢ ለምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ማሕበረሰብ ሰቆቃ የሞላውና ልብ የሚሰብር አሳዛኝ ሃዘን ሆኖብናል። መረጋጋትና ግንዛቤም ለመፍጠር ከማሕበረሰባችን ጋር ሰፋ ያሉ ውይይት አድርገናል።
 
በውይይታችንም ላይ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ፶ ዓመታት ውስጥ የተለያዩ መንግሥታዊ አስተዳደሮችን እንዳስተናገዱና በነዚህ ዓመታት ውስጥ ሕዝባችን አስከፊና ተመሳሳይ ግድያ፣ እንግልት፣ እስርና፣ ስደት ደርሶበትም እንደነበር አጽንዖት ተደርጎበታል።
 
ላለፉት የ፳፯ ዓመታት የሥልጣን እርከኑን በሕግ ሽፋን ስር ጠፍንጎ ለመያዝ ዘር ተኮር ፖለቲካን ዋነኛው የአስተዳደር መመሪያውና ደንብ በማድረግ የሄደባቸው የአስተዳደር ውጤት ትናት ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነትና አንድነት በተምሳሌት የምትታወቀው ውድ ሐገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ የሩዋንዳን አይነት ጽዋ ሊያቀምሷት የዘር ማጥፋት ሾተላቸውን በጋምቤላ በኣኝዋክ ማኀበረሰቦች ላይ ከዛ ወዲህ በቡራዩ፣ በጌድኦ፣ በኦሮሚያ፣በሱማሌ፣ በቤኒ-ሻንጉል፣በአማራ (በቅማንት)፣ በአፋር ወዘተ… በተደጋጋሚ የተፈጸመውና በአሁኑም ሰዓት እየተፈጸመ ያለው አስከፊና አጸያፊ ጭፍጨፋ፣ ግድያ፣ መፈናቀሎችና፣ የንብረት ማውደም ክስተቶች የሚያመላክቱት በሁሉም የሐገሪቷ ክፍሎች ውስጥ በዜጎች መብት፣ በማሕበረሰቡ ማንነት፣ በሐገር ሉዓላዊነት ላይ ያነጣጠረ የሴራና የዘር ፓለቲካ የጋራ ድምር ውጤቶች ናቸው።
 
እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል… እንደሚባለው ኢትዮጵያ ብርቅዬ እሴቶች ያሏትና ለዓለም የጥቁር ሕዝቦች ዋልታና ማገር ሆና እያገለገለች ያለችና የምትኖር ሐገር ናት። ምንም ይህ እውነት የታወቀና ያለ ቢሆንም ድንበር ተሻግሪ ጠላቶቿ ድሮም ነበሩ! አሁንም ወደፊትም ይኖራሉ። ያለፉትን የ፳፯ ዓመታት ጥቃቶችን አስከፊ የሚያደርጋቸው የግለሰቦችና የዜጎች መብት፣ የሕብረተሰብ ማንነት፣ የሐገር ሎዓላዊነት፣ ከሕብረተሰቡ ስነልቦና ጋር ባልተያያዙ እኩይ የፖለቲካ ውሳኔና ሕገ ወጥ ድንጋጌዎች ዜጎች በግድም ሆነ በውድ ለዚሁ እኩይ ተግባራቸው ተገዢ እንዲሆኑ በተለያዩ መንገዶች እየተገፉና እየተገደዱ ስላሉና ስለሚገኙ ነው። ይህም ኢትዮጵያን እንደ ባቢሎን በስም እንጂ በተግባር እንዳትኖር ለማድረግ ከተከፈተባት ከፍተኛ የሴራ ፖለቲካ ባሻገር እጅግ አስከፊና ዘመን ገጠም አጣብቂኝ ውስጥ እንዳለች የሚያሳይ ሲሆን ወደ ጠራው አምባ ዘልቀን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሁላችንንም የአንድነት ጽናት፣ ትዕግስትና፣ መቻል ይጠይቃልና አስተውለን እየተናበብን መስራት ይኖርብናል።
 
አስተውሎ ላዳመጠና ልብ ላለ በየአካባቢው የተፈጸመው ጭፍጨፋ፣ ግድያና፣ ንብረትን ማውደም ስምሪቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የዜጎችን ተቻችሎ በአንድነት መኖርና ማየት በማይሹ ጥቂት ጽንፈኞችና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ አውጥተው ከሚንቀሳቀሱ የውጭ ሃይሎች ጋር ተመሳጥረው በየደረጃው በእቅድ የሚፈጥሩት ለመሆኑ ግልጽ ነው። በየአካባቢውም እየተፈጸመ ያለው ሥርዓት አልበኝነት አንድ ሕብረተሰብ በሌላው ሕብረተሰብ ላይ እያደረሰ ያለው ጥቃት አይደለም። ያ! ቢሆን ኖሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት አስከፊ ጭፍጨፋና የንብረት ማውደም ወንጀል እየተፈጸመ ባለበት ሰዓት ሕብረተሰቡ አብሮ የኖረውን ጎረቤቱን አላስነካም በማለት በርካታዎችን በየጓዳው ደብቆ ባልተከላከለና ሕይወታቸውን ባላተረፈም ነበር። ይህም አንዱ የአንድነታችንና የማንነታችን መገለጫ ምልክት ሲሆን በሌላ በኩል በጽንፈኞች ታስቦና በከፍተኛ ደረጃ ታቅዶና ተቀነባብሮ የተፈጸመ ለመሆኑ በርካታ ምልክቶች እየታዩ ና እየወጡ ነው።
 
ይህ ድርጊት እኛ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰብዓዊ መብት የሚከራከሩ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን በጣም አሳዝኗል። ይህን አጠቃላይ ሁኔታ አስመልክቶ በሂውስተን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ የአንድነት ማሕበር (ኢሕአማ) ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጊዊችንና መመሪያዎችን ለማየት ሞክሯል። በዋነኛነት የዓለም አቀፍ የሰው ልጆች የመብት አስከባሪ ፍርድ ቤት (The International Court of Justice , ICJ) የዘር ማጥፋት ወንጀልን (genocide) አስመልክቶ በአንቀጾቹ ያስቀመጣቸውን ሁለት ተያያዥና ዓበይት ነጥቦችን በግለሰብ፣ በቡድን፣ በማኅበረሰብ፣ በጎሳ፣ በብሔረሰብ፣ በተለያዩ የእምነት ተከታዮችና፣ በሕፃናት ላይ የሚደርሱትን፥
 
፩ የስነ-ልቦና ጫና፥
ከላይ በተዘረዘሩት ላይ በተወሰነም ሆነ ወይም በአብዛኛው ክፍሎች ላይ የሚደረግ ማንኛውም አይነት የስነ-ልቦና ጫናን በተመለከተ
 
፪ የአካል ላይ ጫና፥
ይህ አምስት መስፈርቶችን አካቷል እነዚም፥
1. ከላይ ከተጠቀሱት ዝርዝር ውስጥ ዓባል፣ ወገን፣ ተጠሪ የሆኑትን የገደለ
2. በሰውነታቸው ወይም በስነ-ልቦናቸው ላይ አሰከፊ አደጋና ጥቃት ያደረሰ
3. ለእራሱ እኩይ ተግባር አውቆና አቅዶ በማስገደድና እንዲቀበሉት ጫና በማድረግ ከላይ በተጠቀሱት ዝርዝር የሕብረተሰቡ ክፍሎች ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የአካል ጉዳት፣ የሰውን አካል ቆራርጦ የመለያየት ድርጊት የፈጸመ
4. ከላይ በተዘረዘሩት ክፍሎች ላይ ተፈጥሮ ያደላቸውን የዘር ማፍራት ሂደት በማንኛውም አይነት መለኪያ ዘር እንዳያፈሩ የሚደረጉ ጫናዎችና ተግባራትን የፈጸመ
5. በሃይልና በግድ ልጆችን ከቤተሰቦቻቸውና ከኖሩበት አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሄዱ፣ እንዲሰደዱ ያደረገና የተባበረ ፍርድ ቤቱ (The International Court of Justice , ICJ) ከላይ የተጠቀሱትን ዝርዝሮች የፈጸመና አባሪ ሆኖ የተሳተፈ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ወይም ተቋም በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ደንግጎ አስፍሯል።
 
ችግርና መከራ ብልህነትንና ማስተዋልን ይፈጥራልና ዓያትና ቅድመ ዓያቶቻችን ያቆዩልንን የአብሮ መኖር በዓለም ዙሪያ ወግና ባህሎቻችንን ምርኩዝና መመሪያ በማድረግ ወደፊት ተመሳሳይ ተግባር ዳግም እንዳይፈጠር ከጎጠኝነት ትርክት ወጥተን በመከባበር ኢትዮጵያውነት ላይ ወርቃማ ጊዜያችንና፣ ሕብረታችንን በማሰባሰብ ለበሬ ወለደ ተራኪዎች ጆሮ ሳንሰጥ የሌላውን ቁስል የእኛ ቁስል ነው በሚል መንፈስና ግንዛቤ እራሳችንን አዘጋጅተን ሐገርንና ሕዝብን መታደግ ይኖርብናል።
 
እኛ ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ አለች ወደፊትም ትኖራለች! ያም ሆኖ እንደ ሰውነታችን ሰው የሚያሰኘንና ኢትዮጵያን የሚያሻግር ስራ ሰርተን ስናልፍ ስራችን ለልጆቻችን የመልካም ስራ መመሪያ ሆኖ በታሪካቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው ተከብረውና ተወደው በማንነታቸውም አንገታቸውን ሳይደፉ ቀና ብለው ይኖራሉ።
 
ይህን ዓይነት ሥርዓተ አልበኝነትና ያልተገራ አስተሳሰብ የተጠናወተውን ተግባር ሁላችንም መጸየፍና ተባብረን ለችግሩ መፍትሔና ወደፊትም እንዳይደገም በጋራ እየተናበብን መስራት ይኖርብናል። በዓለማችን ውስጥ በመርዘኛና በዘረኛ ተግባሮች በልጽጎ በሰላም የሚኖር ሃገር የለም። ከዚህ መሰረታዊ እውነት በመነሳት በሂውስተን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ የአንድነት ማሕበር (ኢሕአማ) የዓለም አቀፍ የሰው ልጆች መብት ዋስትናና ድንጋጌን ዋቢ በማድረግ ለችግሩ መፍትሔ ያመጣሉ ብሎ ያሰባቸውን ፍሬ ሃሳቦች እንደሚከተለው በዝርዝር አስቀምጧል።
 
1. ከሁሉም በፊት መንግሥት በሐገራችን የተፈጠረውን ይህን አሰቃቂ ሁኔታ ለግሉ የፖለቲካ ፍጆታ እንዳያውለው ግልጽ ሆኖ በሃገሪቷ ውስጥ የሕግ የበላይነት እንዲኖር ከፍተኛ ጥረት ማድረግና የተጠረጠሩ ግለሰቦች በአስቸኳይ ለሕግ የሚቀርቡበትን ሂደት ማፋጠን ይጠበቅበታል።

2. ከየአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በአስቸኳይ መንግሥት ወደ ቀድሞው መኖሪያቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን እንዲያመቻላቸው።

3. መንግሥት ንብረታቸው የወደመባቸውን ዜጎች ተመጣጣኝ ካሳ በመስጠት የመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም እንዲያወጣ።

4. መንግሥት ወላጆቻቸውን ላጡ ልጆች በአስቸኳይ ልዩ የሆነ መጠለያና ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው።
5. ለመፍትሄዎቹ ታማኝነት መንግሥት ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን በማቋቋም ጉዳዩቹ በአስቸኳይ እንዲታይ እንዲያደርግ።

6. በሐገርና በውጭ ሐገር ውስጥ ባሉ ኢትዮጵያዊያን መካከል የነፃ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ውይይት እንዲካሄድ ማመቻቸትና ማሳወቅ።

7. ዘር ላይ አተኩረው የሚሰነዘሩ ማንኛውም ዓይነት የጥላቻ ትርክቶችና ዘገባዎች ላይ መንግሥት የማያወላዳ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ።

8. ለሩዋንዳው የዘር እልቂት ዋንኛ መሳሪያ የሆነው ዘርን መገለጫ አድርገው የያዙት የመታወቂያ ወረቀት ነበር። አሁንም ኢትዮጵያዊያን እንዲይዙ የተደነገገባቸውን ዘር ተኮር የመታወቂያ ካርድ በአስቸኳይ በሁሉም ክፍሎች ውስጥ እንዲቆም ምክር ቤቱ በአዋጅ ድንጋጌ እንዲያወጣ እናሳስባለን።

9. በሰላማዊ መንገድ ለዲሞክራሲ ለሚታገሉና በብሔራዊ አንድነታችን ዙሪያ ለሚያቀነቅኑ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች መንግስት አስፈላጊውን ደጋፍ እንዲያደርግላቸው። ያልተጠበቀና መሰረት የሌለው መንገላታት፣ እስራት፣ውጣ ውረድ እንዳይደርስባቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል

10. በሁሉም የሐገሪቷ ክፍሎች ውስጥ ዜጎችን በማንነታቸውና በሃይማኖታቸው እየተመረጡ ግድያና የንብረት ማውደም ወንጀል የሰሩ፣ ግድያውንና ጥፋቱን የጠነሰሱ፣ ስልትና እቅድ ነድፈው በማስተባበር አቅጣጫና መመሪያ የሰጡ፣ በአጠቃላይ በሰው ሕይወትና በንብረት ማውደም የተሳተፉትን በሙሉ መንግሥት ለመመለከተው የሕግ አካል ጉዳዩ ያገባናል ብለው ለሚንቀሳቀሱ ወገኖች ድጋፍና አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ እናሳስባለን።
 
በዚህ አሳዛኝና አጸያፊ ተግባር የሞቱትን ዓምላክ አጸደ-ገነትን ያውርስልን እያልን ለወዳጅ ዘመድ ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ያድልልን፣ ለመላው ሐገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ውድ ሐገራችን ሰላምን እንመኛለን።
 
ሒውስተን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ የአንድነት ማሕበር (ኢሕአማ)
 
*********************************************************************
 
ማሳሰቢያ፥
የዚህ መግለጫ ግልባጭ
 
ለተከበሩ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ (ዶ/ር), ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
 
እንዲሁም ለሚከተሉት የኢትዮጵያ የመንግስት ተቋማት ተልኳል፦
 
ለተከበሩ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
አፈ ጉባኤ ለተከበሩ አቶ ታደሰ ጫፎና
 
ለተከበሩ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ
 
ለተከበሩ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ የሠላም ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት ክብርት ሙፈሪያት ካሚል